አዞዎቹ (Crocodiles)

Wednesday, December 11, 2013 ·

---አፈንዲ ሙተቂ
----


ሰሞኑን ከዚያ ትውልድ አውራዎች ጋር ነበር፡፡ ለህዝብ መብት መከበር ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙትን ፋኖዎች በጥቂቱ ዘክረናል፡፡ የነዚያ ፋና ወጊ አብዮተኞች ዋነኛ ምንጭ ሆኖ ያገለገለው “አዞዎቹ” የሚባለው የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ ተማሪዎች ቡድን እንደነበር ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “መሬት ላራሹ” በማለት መስበክ የጀመሩት የአዞዎቹ ቡድን አባላት እንደሆኑ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡

የ“አዞዎቹ” ቡድን ምስረታ የተጠነሰሰው ገብሩ ገብረ ወልድ በሚባለው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር፡፡ ዘመኑም በ1955 ገደማ ነው፡፡ ገብሩ ገብረወልድ ቀደም ባለው ዘመኑ የዓለማያ (ሀረማያ) እርሻ ኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡ ዘርዑ ክሕሸን የሚባለው ተማሪም ከርሱ ጋር ይማር ነበር፡፡ ሁለቱ ተማሪዎች በ1954 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛወሩ፡፡ ከዓመት በኋላም በገብሩ ጠንሳሽነትና በዘርዑ ተባባሪነት ማርክሳዊ ርዕዮት የሚያጠኑበትን ቡድን መሰረቱ፡፡ ከነርሱ ጋር ተቀራራቢ ሀሳብ የነበራቸውን ሌሎች ተማሪዎችንም መሳብ ጀመሩ፡፡ በዚህ መሰረት የቡድኑ ቀዳሚ አባላት የሆኑት
1. ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)
2. ስዩም ወልደዮሐንስ
3. አበራ ዋቅጅራ
4. ዮሐንስ ስብሐቱ ናቸው፡፡

በማስከተልም የነርሱን ዓላማ የሚደግፉ በርከት ያሉ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ የአዞዎቹ ቡድን መሰረቱን ማስፋት ጀመረ፡፡ በ1956 የተማሪ ማህበር አመራር አባላት የነበሩት ብርሃነ መስቀል ረዳ እና እሸቱ ጮሌ ከቡድኑ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ሚካኤል አበበ፣ ታዬ ጉርሙ እና ሐብቴ ወልደ ጊዮርጊስ የአዞዎቹ አባል ሆኑ፡፡
*****
የአዞዎቹ ቡድን ጅምሩ ላይ የጥቂቶች ስብስብ ነበር፡፡ እያደር ግን ስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ የሆነ ሁሉ የሚሰባሰብት የጋራ ማህበር ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ ቡድኑ ከ1960ዎቹ መግቢያ ጀምሮ “አዞዎቹ” በሚለው ስም መጠቀሙን ቢያስቀረውም በአዞዎቹ የተዘረጋው የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ አብዮተኛ ተማሪዎች መስመር እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሰረት ከ1950ቹ መጨረሻ ጀምሮ የአዞዎቹ መስመር ተከታይ በመሆን በንቅናቄው ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው አብዮተኛ ተማሪዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

1. ዋለልኝ መኮንን
2. ጥላሁን ግዛው
3. ጸጋዬ ገብረ-መድህን (ደብተራው)
4. ገዛኽኝ መኮንን
5. ተካልኝ ወልደ አማኑኤል
6. ጌታቸው ሀብቴ
7. ታምራት ከበደ
8. ሄኖክ ክፍሌ
9. ዳዊት ስዩም
10. ጸሎተ ህዝቅያስ
11. ሙሐመድ ማሕፉዝ
12. በድሩ ሱልጣን
13. ዳዊት ህሩይ
14. ተስፉ ኪዳኔ
15. ዮሐንስ በፍቃዱ
16. አማኑኤል ዮሐንስ
17. ሙሉጌታ ስልጣን
18. መስፍን ሐብቱ
19. አያሌው አክሎግ
20. ጌታቸው ሻረው
21. ፋንታሁን ጥሩነህ
22. ይርጋ ተሰማ
23. አባይ አብርሃ
24. መስፍን ካሱ
25. ዮሐንስ ብርሃኔ
26. ብርሀኔ ኢያሱ
27. ወርቁ ገበየሁ
28. እሸቱ አራርሶ
29. ኢያሱ ዓለማየሁ
30. ብንያም አዳነ
31. ገዛኽኝ እንዳለ
32. ዮሴፍ አዳነ
33. አብዱል መጂድ ሁሴን
34. አብዲሳ አያና
35. ሀይለእየሱስ ወልደሰንበት
36. ማርታ መብራህቱ
37. ታደለች ኪዳነ ማሪያም
38. ተስፋዬ ቢረጋ
39. ገብሩ መርሻ
40. ታሪኩ ደብረ ጽዮን
41. ግርማቸው ለማ
42. ጌታቸው ማሩ
43. መለስ ተክሌ
44. ግደይ ገብረዋህድ
45. ረዘነ ታደሰ
46. አሰፋ እንደሻው
47. ሳሙኤል አለማየሁ
48. መላኩ ማርቆስ
49. ወርቁ ገበየሁ

ከላይ በቀረበው ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሱት በሙሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከ1962 በፊት በነበረው ጊዜ የተማሪዎቹ ዋነኛ የትግል ስልት በተቃውሞ ሰልፍና በህትመት መድረኮች ስርዓቱን ማስጨነቅ ነበር፡፡ ህዝቡንና አብዮታዊ ምሁራንንም በተቃውሞው ጎራ ለማሰለፍ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከ1962 በኋላ ግን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ይህንን ስልት እርግፍ አድርገው በመተው ልዩ ልዩ የውይይት ክበቦችን እየመሰረቱ ስለሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም እና ስለ ድርጅት ምስረታ መወያየት ጀመሩ፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ከሀገር ተሰደዱ፡፡ በሀገር ውስጥ የቀሩት ተማሪዎች በውጪ ሀገር ካሉ የተማሪ ማህበር አባላትና ስደተኛ ተማሪዎች ጋር በመቀናጀት የስርዓት ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ መሻት ጀመሩ፡፡ በስተመጨረሻም በልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅት ስር በመሰለፍ ታገሉ፡፡ ይሁንና በጣም የሚበዙት ያሰቡትን ከግብ ሳያደርሱ ከዚህች ዓለም ተሰናበቱ፡፡
*****
አዞዎቹ በዚህ ዘመን በአብዛኛው በህይወት የሉም-ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ብዙዎቹ የሞቱት በአብዮቱ አፍላ ወቅት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ተይዘው ነበር የተረሸኑት፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ከደርግ አሳሾች ሲሸሹ ነው የተገደሉት፡፡ ጥላሁን ግዛውና ዋለልኝ መኮንንን የመሳሰሉት ግን ቀደም ብለው በአጼ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ አንዳንዶች በዚያው ዘመን ዱር ገብተው ሲዋጉ ህይወታቸው አልፏል፡፡ እንደ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ፣ ዘሩ ክሕሸን እና አብዱል መጂድ ሑሴንን የመሳሰሉት ደግሞ በህመም ምክንያት ሞተዋል፡፡ በዚህ ዘመን በህይወት መኖራቸው የሚታወቀው የአዞዎቹ ቡድን አባላት

1. ሀይሉ ገብረዮሐንስ (በሀገረ ስዊዲን የሚኖሩ)
2. ገብሩ ገብረወልድ (በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩት)
3. አበራ ዋቅጅራ (አሜሪካ የሚኖሩ)
4. ኢያሱ ዓለማየሁ (ፈረንሳይ ሀገር የሚኖሩ)
5. አብዲሳ አያና (አውሮጳ የሚኖሩ)
6. ገብሩ መርሻ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩ)
7. ጸጋዬ ገብረመድህን (መቀሌ እስር ቤት ይገኛል ተብሎ የሚጠረጠር) ናቸው፡፡
*****
አፈንዲ ሙተቂ
ታህሳስ 2/2006

(እንደ ማስታወሻ፡ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ሰናይ ልኬ፣ ነገደ ጎበዘ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ ክፍሉ ተፈራ የመሳሰሉት አብዮተኞች የአዞዎቹ ቡድን አባላት አልነበሩም፡፡ እነዚያኛዎቹ ትምህርታቸውን በውጪ በሚከታተሉበት ወቅት ነው ወደ ንቅናቄው የገቡት)፡፡

0 comments:

ስለጦማሩ

ከታህሳስ 1966 ዓ/ም በፊት ስለነበረው ስር ነቀል የተማሪዎች ንቅናቄ እና ንቅናቄው ስላራመደው አስተሳሰብ የሚፃፍበት፣የተፃፉ መጣጥፎች የሚጋሩበትእንዲሁም በአጠቃላይ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ የሚቆዘምበት ጦማር ነው።