ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ዛሬ ህዳር 29 ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በመላው ኢትዮጵያ ይከበራል፡፡ የበዓሉ መከበር ክፋት የለውም፡፡ዋናው ነገር ግን የብሔሮችና ብሔረሰቦችን መብት በተግባር ማረጋገጥ ነው፡፡ ብሔሮች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ የሚደረገው ጥረት ከፕሮፓጋንዳ በጸዳ መልኩ ገቢራዊ ቢሆን ጠቀሜታው ለሁሉም ነው፡፡
የመንግስት ባለስልጣናት የብሄሮችና ብሔረሰቦች በዓል በዚህ ቀን እንዲከበር የተወሰነው ህገ-መንግሥቱ የጸደቀበት ቀን ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን ታሪክን የበለጠ ቢመረምሩ ከዚህ የበለጠ አሳማኝ ምክንያት ያለው ዕለት ያገኙ ነበር ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ ያህል የብሄሮችን እኩልነት የሚጠይቅ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በዚሁ የህዳር ወር ውስጥ ነበር፡፡ የሚለጥቀው የታህሳስ ወር መጀመሪያ ደግሞ ያንን ለየት ያለ ጽሑፍ በከፍተኛ ድፍረትና ልበ ሙሉነት የጻፈው ጀግና አብዮታዊ የተሰዋበት ወቅት ነበር፡፡
*****
ታህሳስ 10/1964፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መለስተኛ አውሮፕላን የሀገር ውስጥ በረራ ለማድረግ ከቦሌ አየር ማረፊያ ሊነሳ ነው፡፡ በአውሮፕላኑ የሚጓዙ መንገደኞች ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ሰባት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረዋል፡፡ የበረራው ሰዓት ሲደርስ አውሮፕላኑ ከመሬት ተነሳ፡፡ በሰማይ ላይ ገብቶ መብረር ሲጀምር ግን ያልታሰበ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ እነዚያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አውሮፕላኑን በቁጥጥራቸው ስር ማዋላቸውን አስታወቁ፡፡ እነርሱ ወደሚፈልጉት ሀገር እንዲበሩም አብራሪዎቹን አዘዟቸው፡፡ ተማሪዎቹ የጠለፋ እወጃውን ካሰሙ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ አውሮፕላኑን ከጠለፋ እንዲታደጉ የታዘዙ ኮማንዶዎች በቀጥታ በጠላፊዎቹ ላይ በማነጣጠር ተኮሱባቸው፡፡ ስድስት ጠላፊዎች ተገደሉ፡፡ አንዲት ጓደኛቸው ደግሞ በከባድ ሁኔታ ቆሰለች፡፡ የአውሮፕላኑ ወለል በሙታኑ ደም ታጠበ፡፡
*****
በዚያች ዕለት የሞተው ታዋቂው የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ ዋለልኝ መኮንን ነበር፡፡ ከርሱ ጋር የተገደሉትም ማርታ መብራህቱ፣ ጌታቸው ሀብቴ፣ ተስፋዬ ቢረጋ፣ ዮሐንስ በፈቃዱ እና አማኑኤል ዮሐንስ ናቸው፡፡ እነዚያ ወጣቶች አውሮፕላኑን ለመጥለፍ የሞከሩት የስርዓቱ ክትትል መፈናፈኛ ስላሳጣቸው ነው፡፡ ዓላማቸው ወደ ውጪ ከኮበለሉት ጓደኞቻቸው ጋር በመቀላቀል ለስር-ነቀል ለውጥ የሚታገል ድርጅት መመስረት ነበር፡፡ ከድርጅቱ ምስረታ በኋላም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ትግሉን በየአቅጣጫው ለማፋፋም አስበዋል፡፡ ሆኖም እንደተመኙት አልሆነላቸውም፡፡ አውሮፕላን ለመጥለፍ ማቀዳቸው ቀደም ብሎ ተጠቁሞ ስለነበር የጸጥታው ክፍል በአየር ላይ አፍኖ አስቀራቸው፡፡
*****
ከላይ በተገለጸው አሳዛኝ ገቢር (ትራጄዲ) ህይወቱ የተቋጨው ዋለልኝ መኮንን በወሎ ክፍለ ሀገር የሳይንት (ቦረና) አውራጃ ተወላጅ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደሴ ከተማ በሚገኘው ታሪካዊው ወይዘሮ ስሒን ት/ቤት ነው ያጠናቀቀው፡፡ በ1958 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ እጅግ የተለየ አብዮታዊ ሆነ፡፡ በ1959 በዩኒቨርሲቲው በተደረገው የግጥም ውድድር “ሙት ወቃሽህ መጣው” በሚለው ግጥም አንደኛ ወጥቷል፡፡ ዋለልኝ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት ይዘጋጅ በነበረው የታገል መጽሔት ከማንም በላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ በህቡዕ የሚዘጋጁ ጽሑፎችንም እያዘጋጀ ያሰራጭም ነበር፡፡ በተለይ “አዞዎቹ” የሚባለው የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ የተማሪዎች ስብስብ በአቋም ደረጃ የተስማማባቸውን ሀሳቦች በጽሑፍ እያቀናበረ የሚያዘጋጀው እርሱ እንደነበር በያኔው እንቅስቃሴ የተሳተፉትም ሆነ የዘመኑን ታሪክ ያጠኑ ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡
ከዋለልኝ ጽሑፎች መካከል ዝነኛ የሆኑት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ከላይ የጠቀስኩትና ህዳር 10/1961 በታተመው “ታገል መጽሔት” ላይ የወጣው “የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በ1962 የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው ሲገደል የአጼው ስርዓት በተማሪዎቹ ላይ ያደረገውን ዛቻ በመቃወም “ለአዋጁ አዋጅ” በሚል ርዕስ በህቡዕ ጽፎ የበተነው ጽሑፍ ነው፡፡ ዋለልኝ በጽሑፎቹ ሳቢያ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታስሯል፡፡ በተለይ “ለአዋጁ አዋጅ”ን የጻፈው እርሱ መሆኑ ሲታወቅ በችሎት ፊት ቀርቦ አምስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል (ሆኖም ተማሪዎች ባደረጉት ከፍተኛ የተቃውሞ ጫና ከዓመት በኋላ ተፈትቷል)፡፡
ከ1962 በኋላ ሁለት ክስተቶች የተማሪውን ንቅናቄ አቅጣጫ ቀይረውታል፡፡ እነዚህም ከስርዓቱ የሚደረገው አፈና መጠናከር እና የድርጅት ምስረታ ጥያቄ መቀስቀስ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተቃውሞ ሰልፍ ይልቅ የጥናት ክበቦችን እየመሰረቱ መወያየቱን መረጡ (የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በተቃውሞ ቀጠሉ)፡፡ ዋለልኝም በውይይት ክበቡ በሚያደርገው ጥናት ላይ አተኮረ፡፡ ከሀገር ተሰደው በአልጄሪያ ከሚገኙት እነ ብርሀነ መስቀል ረዳ ጋር በሚያደርገው የደብዳቤ ልውውጥ አማካኝነት ሰፊ መሰረት ያለው ድርጅት ለመመስረት በሚደረገው ውይይትም ውስጥ ይሳተፍ ነበር፡፡ በታህሳስ ወር 1964 ውጪ ካሉት ጓደኞቹ ጋር ለመቀላቀል ሲል አውሮፕላን ጠለፈ፡፡ ሆኖም ካሰበው ሳይደርስ በአውሮፕላኑ ውስጥ ተገደለ፡፡
*****
ዋለልኝ ከያኔው የተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች መካከል አንድ የሚለይበት ነገር አለው፡፡ ይኸውም ልዩ ልዩ የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አርአያ የሚታይ መሆኑ ነው፡፡ ኢህአፓ፣ ህወሐት፣ ኦነግ፣ ሻዕቢያ፣ መኢሶን፣ ወዘተ… ሁሉም ለርሱ በጎ አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ ታዲያ በርሱ ታሪክ ላይ የሚደረገው ሽሚያም በጣም የጠነከረ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታሪኩን ከራሳቸው ድርጅት ጋር ለማቆራኘት ይሞክራሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው የርሱና የጓደኞቹ አሰላለፍ ሲገመገም ግን ዋለልኝ ኢህአፓን ከመሰረቱ ወጣቶች ጋር ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የነበረው ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ኢህአፓን የመሰረቱትም የርሱ የቅርብ ጓደኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዋለልኝ በህይወት ቢሰነብት ኖሮ የዚሁ ድርጅት አካል ይሆን ነበር ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡
*****
ዋለልኝ መኮንን ከብዙ በጥቂቱ ይህ ነበር፡፡ ወደፊት ሰፋ ባለሁኔታ ስለርሱ እጽፋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ እናንተም በበኩላችሁ የምታውቁትን እንድታጋሩን እንጠይቃለን፡፡


0 comments:
Post a Comment